Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 5 · ቀን 23 (ረቡዕ) 📅 Tikimt 4, 2019

ኦሪት ዘጸአት 7, 8, 9 · መዝሙረ ዳዊት 105 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 7

1.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። 2.ያዘዝሁህን ነገር ሁሉ አንተ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ከፈርዖን ጋር ይናገራል። 3.እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ በግብፅ ምድርም ድንቄንና ተአምራቴን አበዛለሁ። 4.ፈርዖንም አይሰማችሁም፥ እጄንም በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴንም የእስራኤልን ልጆች ሕዝቤን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ አገር አወጣለሁ። 5.ግብፃውያንም፥ እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው ባወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆነሁ ያውቃሉ። 6.ሙሴና አሮንም እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7.ፈርዖንንም በተናገሩት ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ሰው ነበረ፥ አሮንም የሰማንያ ሦስት ዓመት ሰው ነበረ። 8.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ሲል ተናገራቸው። 9.ፈርዖን። ተአምራትን አሳዩኝ ሲላችሁ፥ አሮንን። በትርህን ወስደህ እባብ እንድትሆን በፈርዖን ፊት ጣላት በለው። 10.ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በባሮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነች። 11.ፈርዖንም ጠቢባንንና መተተኞችን ጠራ፤ የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ ደግሞ አደረጉ። 12.እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች። 13.እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። 14.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ። 15.ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። 16.እንዲህም ትለዋለህ። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር። በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆም እስከ ዛሬ አልሰማህም። 17.እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፥ ውኃውም ተለውጦ ደም ይሆናል። 18.በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፥ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ። 19.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ውሰድ፥ ደምም እንዲሆኑ በግብፅ ውኆች በወንዞቻቸውም በመስኖቻቸውም በኩሬዎቻቸውም በውኃ ማከማቻዎቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ በለው፤ በግብፅም አገር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል። 20.ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ። 21.በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፥ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም ደሙም በግብፅ አገር ሁሉ ነበረ። 22.የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። 23.ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም። 24.ግብፃውያንም ሁሉ የወንዙን ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ አጠገብ ውኃ ሊጠጡ ቆፈሩ። 25.እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ።

ምዕራፍ 8

1.እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው። ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2.ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤ 3.ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ፤ 4.ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ። 5.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖቹ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አውጣ በለው። 6.አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፥ የግብፅንም አገር ሸፈኑ። 7.ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ። 8.ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ አላቸው። 9.ሙሴም ፈርዖንን። ጓጕንቸሮቹ ከአንተ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ አለው። እርሱም። ነገ አለ። 10.ሙሴም። አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን። 11.ጓጕንቸሮቹም ከአንተ ከቤቶችህም ከባርያዎችህም ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ አለ። 12.ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13.እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ። 14.እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች። 15.ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም። 16.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ በለው። 17.እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ። 18.ጠንቋዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ። 19.ጠንቋዮችም ፈርዖንን። ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። 20.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 21.ሕዝቤንም ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ በባሪያዎችህም በሕዝብህም በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጎች እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጎች ይሞላሉ። 22.በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የዝንብ መንጋ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ። 23.በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ተአምራት ነገ ይሆናል። 24.እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖንም ቤት በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ጠፋች። 25.ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ሂዱ፥ በአገሩ ውስጥ ለአምላካችሁ ሠዉ አላቸው። 26.ሙሴም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችን የግብፃውያንን ርኵሰት እንሰዋለንና እንዲህ ይደረግ ዘንድ አይገባም፤ እነሆ እኛ የግብፃውያንን ርኵሰት በፊታቸው ብንሠዋ አይወግሩንምን? 27.እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እንደሚያዝዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን አለ። 28.ፈርዖንም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ አትሂዱ፥ ጸልዩልኝ አለ። 29.ሙሴም። እነሆ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፥ የዝንቡም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከሕዝቡም ነገ እንዲሄዱ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እንዳይለቅቅ ፈርዖን እንደገና አያታልለን አለ። 30.ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 31.እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ የዝንቡንም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከህዝቡም አስነሣ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም። 32.ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።

ምዕራፍ 9

1.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2.ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል ብትይዛቸውም፥ 3.እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል። 4.እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም። 5.እግዚአብሔርም። ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ። 6.እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። 7.ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም። 8.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9.እርሱም በግብፅ አገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብፅም አገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል አላቸው። 10.ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ። 11.ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል በጠንቋዮችና በግብፃያን ሁሉ ላይ ነበረና። 12.እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው አልሰማቸውም። 13.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14.በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ። 15.አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ 16.ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ። 17.እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን? 18.እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ። 19.በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና አሁን እንግዲህ ላክ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ አስቸኵል። 20.ከፈርዖንም ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤ 21.የእግዚአብሔርንም ቃል ያላሰበ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ። 22.እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ አለው። 23.ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ። 24.በረዶም ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፥ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ ነበረ። 25.በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ፥ የአገሩንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 26.የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም። 27.ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን ጠራ። በዚህ ጊዜ በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም ኃጢያተኞች ነን። 28.የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እለቅቃችሁማለሁ፥ ከዚያም በኋላ በዚህ አትቀመጡም አላቸው። 29.ሙሴም። ከከተማ በወጣሁ ጊዜ እጄን ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር እንደሆነች ታውቅ ዘንድ ነጎድጓዱ ይቀራል፥ በረዶውም ደግሞ አይወርድም። 30.ነገር ግን አንተና ባሪያዎችህ አምላክን እግዚአብሔርን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁ አለው። 31.ገብሱ እሸቶ ተልባውም ኣፍርቶ ነበርና ተልባና ገብሱ ተመታ። 32.ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም። 33.ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ተቋረጠ፥ ዝናቡም በምድር ላይ አልፈሰሰም። 34.ፈርዖንም ዝናቡ በረዶውም ነጎድጓዱም እንደ ተቋረጠ ባየ ጊዜ ኃጢያትን ጨመረ፥ እርሱና ባሪያዎቹም ልባቸውን አደነደኑ። 35.የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደተናገር የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 105

1.ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ።
2.ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። 3.በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። 4.እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።
5
6.ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱን የአፉንም ፍርድ። 7.እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። 8.ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ 9.ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ 10.ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን እንዲሆን አጸና። 11.እንዲህም አለ። ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ገመድ እሰጣለሁ፤ 12.ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች ሲሆኑ ነው። 13.ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ።
14 -
15.የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። 16.በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ። 17.በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ። 18.እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። 19.ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። 20.ንጉሥ ላከ ፈታውም፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው። 21.የቤቱ ጌታ፥ የጥሪቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥ 22.አለቆቹን እንደ ፈቃዱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ። 23.እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ። 24.ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። 25.ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። 26.ባሪያውን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ። 27.የተኣምራቱን ነገር በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረገ። 28.ጨለማን ላከ ጨለመባቸውም፤ በቃሉም ዐመፁ። 29.ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። 30.ምድራቸው የንጉሦቻቸውም ቤቶች በጓጕንቸር ሞሉ። 31.ተናገረ፥ የውሻ ዝንብ ትንኝም በዳርቻቸው መጡ። 32.ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ እሳትም በምድራቸው ተቃጠለች። 33.ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 34.ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥ 35.የአገራቸውንም ለምለም ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ። 36.የአገራቸውንም በኵር ሁሉ፥ የጕልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ። 37.ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ ደዌ አልነበረም። 38.ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት። 39.ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት ያበራላቸው ዘንድ ዘረጋ። 40.ለመኑ፥ ድርጭትንም አመጣላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። 41.ዓለቱን ሰነጠቀ፥ ውኃውም ፈሰሰ፤ ወንዞች በበረሃ ሄዱ፤ 42.ለባሪያው ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን አስቦአልና። 43.ሕዝቡንም በደስታ የተመረጡትንም በእልልታ አወጣ። 44.የአሕዛብንም አገሮች ሰጣቸው፥ የወገኖችንም ድካም ወረሱ፥ 45.ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዓቱንም ይፈልጉ ዘንድ። ሃሌ ሉያ

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 1

1.በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ 2.ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 3.በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4.ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። 5.በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። 6.በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። 7.በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። 8.ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። 9.በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ 10.በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። 11.እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። 12.ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። 13.እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ 14.እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። 15.ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥ 16.ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ 17.የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ።
18 -
19.ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤
20 -
21.ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ 22.ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። 23.እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።
♫
Listen to the reading 5 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 7
ኦሪት ዘጸአት Chapter 8
ኦሪት ዘጸአት Chapter 9
መዝሙረ ዳዊት Chapter 105
ወደ ኤፌሶን ሰዎች Chapter 1
Swipe to browse chapters
Listen 5