Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 5 · ቀን 22 (ማክሰኞ) 📅 Tikimt 3, 2019

ኦሪት ዘጸአት 4, 5, 6 · ወደ ገላትያ ሰዎች 6

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 4

ለሙሴ የተሰጡ ምልክቶች

1.ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ። 2.እግዚአብሔርም፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው።
3.እግዚአብሔርም፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው።
ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ።
4.እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች። 5.እግዚአብሔርም “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው። 6.እግዚአብሔርም ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። 7.“አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች። 8.እግዚአብሔርም፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ። 9.እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።” 10.ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ጌታ ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋራ ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው። 11.እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? 12.በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። 13.ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው። 14.በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል። 15.ለርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ ረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። 16.አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል። 17.ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።”
ሙሴ ወደ ግብጽ ተመለሰ
18.ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብጽ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው።
ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው።
19.ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብጽ ሂድ” አለው። 20.ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብጽ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርም በትር በእጁ ይዞ ነበር። 21.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብጽ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። 22.ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ 23.ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ” 24.ሙሴ በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። 25.ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። 26.ስለዚህም እግዚአብሔር ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው። 27.እግዚአብሔር አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። 28.ሙሴም እግዚአብሔር እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው። 29.ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ 30.አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31.ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኛቸውና መከራቸውን እንዳየ በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።

ምዕራፍ 5

ጭድ አልባ ሸክላ

1.ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይላል” አሉት። 2.ፈርዖንም “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር ማነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም አልለቅም” አለ። 3.እነርሱም፣ “የዕብራውያን አምላክ ለእኛ ተገልጦልናል፤ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳው ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ አለዚያ ግን በመቅሠፍት ወይም በሰይፍ ይመታናል” አሉት። 4.የግብጽ ንጉሥም፣ “እናንተ ሙሴና አሮን፤ ለምንድን ነው ሕዝቡን ሥራ የምታስፈቱት? በሉ እናንተም ወደየሥራችሁ ተመለሱ!” 5.ፈርዖንም፣ “እነሆ፤ አሁን የምድሪቱ ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፤ እናንተም እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” አለ። 6.በዚያ ዕለት ፈርዖን ለባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና ለሕዝቡ አለቆች እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ 7.“ለጡብ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ጭድ ካለበት ቦታ ሄደው ራሳቸው ያምጡ እንጂ ከእንግዲህ እናንተ እንዳታቀርቡላቸው። 8.ሆኖም ቀድሞ በሚያቀርቡት ሸክላ ልክ ሠርተው እንዲያቀርቡ አድርጓቸው። የሥራ ድርሻቸውን አትቀንሱ። ሰነፎች ናቸው፤ ‘ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት እንሠዋ’ የሚሉትም ለዚህ ነው። 9.ለሐሰት ወሬ ስፍራ ሳይሰጡ ተግተው እንዲሠሩ ሥራውን አክብዱባቸው።” 10.ከዚያም የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና አለቆቹ ወጥተው ለሕዝቡ፣ “ፈርዖን የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእንግዲህ ጭድ አልሰጣችሁም፤ 11.ሂዱና የራሳችሁን ጭድ ከየትም ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራ ድርሻችሁ ግን ከቶ አይቀነስም’ ” አሉ። 12.ስለዚህም ሕዝቡ በጭድ ፈንታ ገለባ ለመሰብሰብ በግብጽ ምድር ሁሉ ተሰማሩ። 13.የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹም “በየዕለቱ መሥራት የሚገባችሁ ሥራ ቀድሞ ጭድ ስናቀርብላችሁ ከምትሠሩት ሥራ ማነስ የለበትም” እያሉ ያጣድፏቸው ነበር። 14.የሥራው የቅርብ ኀላፊዎች ተደርገው በፈርዖን የባሪያ ተቈጣጣሪዎች የተመደቡት እስራኤላውያንም፣ “የትናንቱንም ሆነ የዛሬውን ሸክላ ሥራ ድርሻችሁን እንደ ቀድሞው ለምን አላሟላችሁም?” እየተባሉ ይጠየቁና ይገረፉ ነበር። 15.ከዚያም ሥራውን በቅርብ ሆነው የሚቈጣጠሩት እስራኤላውያን ኀላፊዎች ፈርዖን ፊት ቀርበው እንዲህ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፤ “እኛን ባሮችህን እንደዚህ የምታደርገን ለምንድን ነው? 16.ለእኛ ለባሮችህ ጭድ ሳያቀርቡልን ሸክላ ሥሩ ይሉናል፤ ጥፋቱ የገዛ ሰዎችህ ሆኖ ሳለ እኛ ባሮችህ ግን እንገረፋለን።” 17.ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ልግመኞች! እናንተ ልግመኞች! እየደጋገማችሁ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔር እንሠዋ’ የምትሉት ለዚህ ነው። 18.በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ፤ ምንም ጭድ አይሰጣችሁም፤ ያም ሆኖ ግን የተመደበላችሁን ሸክላ ማምረት አለባችሁ።” 19.እስራኤላውያን ኀላፊዎችም፣ “በየቀኑ የምትሠሩት ሸክላ ቍጥሩ ቀድሞ ከሚሠራው ሸክላ ማነስ የለበትም” ተብሎ ሲነገራቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተረዱት። 20.ከፈርዖን ዘንድ እንደ ተመለሱ ሲጠብቋቸው የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አግኝተው፣ 21.“እግዚአብሔር ይይላችሁ፤ ይፍረድባችሁም፤ ፈርዖንና ሹማምቱ እንዲጠየፉን አደረጋችሁ፤ እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ ሰጣችኋቸው” አሏቸው።

እግዚአብሔር እንደሚታደግ ተስፋ ሰጠ

22.ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፣ “አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ ያመጣኸው ለምንድን ነው? የላክኸኝ ለዚሁ ነው? 23.በአንተ ስም እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከሄድሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ አበሳ አምጥቷል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አልታደግኸውም” አለው።

ምዕራፍ 6

1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ፤ ከኀያሉ እጄ የተነሣ እንዲሄዱ ይለቅቃቸዋል፤ ከኀያሉም እጄ የተነሣ ከአገሩ ያስወጣቸዋል” አለው። 2.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3.ሁሉን ቻይ አምላክ ሆኜ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ ተገለጥሁላቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በተባለው ስሜ ራሴን አልገለጥሁላቸውም። 4.በእንግድነት የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር እንድሰጣቸው ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። 5.ደግሞም በግብጻውያን ሥር በባርነት ሆነው ያሰሙትን የእስራኤላውያንን የሥቃይ ድምፅ ሰምቻለሁ ኪዳኔንም አስታውሻለሁ። 6.“ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብጻውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ። 7.የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብጻውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ። 8.ከዚያም ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” 9.ሙሴ ይህን ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ ተስፋ ከመቍረጣቸውና ከአስከፊ እስራታቸው የተነሣ ግን አላደመጡትም። 10.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11.“ሂድና ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እስራኤላውያን ከአገሩ እንዲወጡ ይፈቅድላቸው ዘንድ ንገረው።” 12.ሙሴ ግን እግዚአብሔርን፣ “እስራኤላውያን ያልሰሙኝ፣ ፈርዖን እንዴት ይሰማኛል፤ እኔ ለራሴ ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።

የሙሴና የአሮን የትውልድ መዝገብ

13.በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ስለ እስራኤላውያንና ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ለሙሴና ለአሮን ነገራቸው፤ እስራኤላውያንንም ከግብጽ እንዲያወጡ አዘዛቸው። 14.የየቤተ ሰቡ አለቆች እነዚህ ነበሩ፤
የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፣
ሄኖኅ፣ ፈሉስ፣ አስሮን፣ ከርሚ።
እነዚህ የሮቤል ነገድ ናቸው።
15.የስምዖን ወንዶች ልጆች፣
ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል ነበሩ።
እነዚህ የስምዖን ነገድ አባቶች ናቸው።
16.በትውልዳቸው መሠረት የሌዊ ወንዶች ልጆች ስሞች እነዚህ ነበሩ፤
ጌርሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው።
ሌዊ መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ።
17.የጌርሶን ወንዶች ልጆች በትውልዳቸው ሎቤኒና ሰሜኢ ነበሩ። 18.የቀዓት ወንዶች ልጆች
እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮንና ዑዝኤል ነበሩ፤
ቀዓት መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ኖረ።
19.የሜራሪ ወንዶች ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ።
በትውልዳቸው መሠረት የሌዊ ነገዶች እነዚህ ናቸው።
20.እንበረም የአጎቱን እናት ዮካብድን አገባ፤ እርሷም አሮንና ሙሴን ወለደችለት።
እንበረም መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ።
21.የይስዓር ወንዶች ልጆች፣
ቆሬ፣ ናፌግና ዝክሪ ነበሩ።
22.የዑዝኤል ወንዶች ልጆች፣
ሚሳኤል፣ ኤልዳፋንና ሥትሪ ነበሩ።
23.አሮንም የአሚናዳብን ልጅ፣ የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፤ እርሷም ናዳብንና አብዩድን፣ አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት። 24.የቆሬ ወንዶች ልጆች፣
አሴር፣ ሕልቃናና አብያሳፍ ነበሩ፤
እነዚህ የቆሬ ነገድ ጐሣ ናቸው።
25.የአሮን ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ሴት ልጆች አንዷን አገባ፤ እርሷም ፊንሐስን ወለደችለት።
እነዚህ እንደየነገዳቸው የሌዋውያን ጐሣዎች አለቆች ነበሩ።
26.እግዚአብሔር “እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው ከግብጽ አውጡ” ብሎ የነገራቸው አሮንንና ሙሴን ነበር። 27.ስለ እስራኤላውያን ከግብጽ መውጣት፣ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን ያናገሩትም እነዚሁ ሙሴና አሮን ነበሩ። 28.እግዚአብሔር ሙሴን በግብጽ በተናገረው ጊዜ፣ 29.እንዲህ አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የነገርሁህን ሁሉ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው።” 30.ሙሴ ግን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ፈርዖን ምን ብሎ ይሰማኛል? አንደበቴ ኰልታፋ ነው።”

ወደ ገላትያ ሰዎች

ምዕራፍ 6

ለሰው ሁሉ በጎ ማድረግ

1.ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል። ነገር ግን አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። 2.አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። 3.አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል። 4.እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋራ ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል፤ 5.እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋልና። 6.ማንም ቃሉን የሚማር፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ከመምህሩ ጋራ ይካፈል። 7.አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል። 8.ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። 9.በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤ ተስፋ ካልቈረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን። 10.ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ።

አዲስ ፍጥረት መሆን

11.እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ ተመልከቱ! 12.ውጫዊ በሆነ ነገር ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ትገረዙ ዘንድ ሊያስገድዷችሁ ይጥራሉ፤ ይህንም የሚያደርጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ነው። 13.እነርሱ በሥጋችሁ ለመመካት ሲሉ እንድትገረዙ ፈለጉ እንጂ፣ የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን የሚጠብቁ አይደሉም። 14.ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር፣ ሌላ ትምክሕት ፈጽሞ ከእኔ ይራቅ። 15.መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። 16.ይህን ትእዛዝ በሚከተሉ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በሆነው እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። 17.እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። 18.ወንድሞች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋራ ይሁን። አሜን።