Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 5 · ቀን 21 (ሰኞ) 📅 Tikimt 2, 2019

ኦሪት ዘጸአት 1, 2, 3 · ወደ ገላትያ ሰዎች 5

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 1

እስራኤላውያን በጭቈና ሥር

1.ቤተ ሰቦቻቸውን ይዘው ከያዕቆብ ጋራ ወደ ግብጽ የሄዱት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፦ 2.ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ 3.ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ብንያም፣ 4.ዳን፣ ንፍታሌም፣
ጋድና አሴር።
5.የያዕቆብ ዘር ጠቅላላ ብዛት ሰባ ሲሆን፣ ዮሴፍ ግን ቀደም ብሎ በግብጽ ነበረ። 6.ከጊዜ በኋላ ዮሴፍና ወንድሞቹ ያም ትውልድ በሙሉ ሞቱ፤ 7.ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እየተዋለዱ በዙ፤ ቍጥራቸው እጅግ ከመጨመሩም የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሏት። 8.በግብጽም፣ ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ ነገሠ። 9.እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው፤ 10.ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ ጦርነት ቢነሣ ከጠላቶቻችን ጋራ ዐብረው እንዳይወጉንና ከምድሪቱም ኰብልለው እንዳይሄዱ ዘዴ እንፈልግ።” 11.ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት። 12.ነገር ግን ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቍጥር በዛ፤ በምድሪቱም እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው፤ 13.ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታም ያሠሯቸው ጀመር። 14.ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በዕርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብጻውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር። 15.የግብጽም ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን ሴቶች አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤ 16.“የዕብራውያንን ሴቶች በማማጫው ድንጋይ ላይ በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” 17.አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ የግብጽ ንጉሥ ያዘዛቸውን አልፈጸሙም፤ ወንዶቹንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው። 18.ንጉሡም አዋላጆቹን ጠርቶ፣ “ለምንድን ነው ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው?” አላቸው። 19.እነርሱም፣ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጻውያን ሴቶች አይደሉም፤ ብርቱዎች ስለ ሆኑ አዋላጆች ከመድረሳቸው በፊት ይወልዳሉ” ሲሉ ለፈርዖን መለሱለት። 20.ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለአዋላጆቹ መልካም ሆነላቸው፤ ሕዝቡም በቍጥር እየበዛና እያየለ ሄደ። 21.አዋላጆቹም እግዚአብሔርን በመፍራታቸው ቤተ ሰብ ሰጣቸው። 22.ፈርዖንም፣ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉት፤ ሴት ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት ትኑር” ሲል ሕዝቡን አዘዘ።

ምዕራፍ 2

የሙሴ መወለድ

1.በዚያ ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ። 2.እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። 3.ከዚያ በላይ ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ ግን የደንገል ቅርጫት ወስዳ፣ በዝፍትና በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም በውስጡ አስተኝታ ቅርጫቱን አባይ ወንዝ ዳር ቄጠማ መካከል አስቀመጠችው። 4.የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ታይ ነበር። 5.በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅ ልትታጠብ ወደ አባይ ወንዝ ወረደች፤ በምትታጠብበትም ጊዜ ደንገጥሮቿ በወንዙ ዳር ወዲያና ወዲህ ይሉ ነበር፤ በቄጠማውም መካከል የተቀመጠ ቅርጫት አይታ ከደንገጥሮቿ አንዷን እንድታመጣው ላከቻት። 6.ቅርጫቱን ስትከፍተው ሕፃኑን በውስጡ አየች፤ ያለቅስ ስለ ነበርም ዐዘነችለትና፣ “ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ መሆን አለበት” አለች። 7.የሕፃኑ እኅት ለፈርዖን ልጅ፣ “ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ሞግዚት ላምጣልሽን?” አለቻት። 8.የፈርዖንም ልጅ፣ “መልካም፣ ሂጂ” አለቻት። ልጅቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ይዛ መጣች። 9.የፈርዖንም ልጅ ሴቲቱን፣ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝ እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴትዮዋም ሕፃኑን ወስዳ አሳደገችው። 10.ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ ልጇም ሆነ፤ እርሷም፣ “ከውሃ አውጥቼዋለሁና” ስትል ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው።

ሙሴ ወደ ምድያም ምድር ሸሸ

11.ሙሴ ካደገ በኋላ አንድ ቀን ወገኖቹ ወደሚገኙበት ስፍራ ወጣ፤ በዚያም ተገድደው ከባድ ሥራ ሲሠሩ ተመለከተ፤ ዕብራዊ ወገኑንም አንድ ግብጻዊ ሲደበድበው አየ። 12.ሙሴም አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ ግብጻዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው። 13.በማግስቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው። 14.ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቋል!” በማለት ፈራ። 15.ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። 16.የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ውሃው ጕድጓድ መጥተው የአባታቸውን በጎች ውሃ ለማጠጣት ገንዳውን ሞሉት። 17.እረኞችም መጥተው ሴቶቹን ሲያባርሯቸው ሙሴ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ተከላከለላቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። 18.ሴቶቹም ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ፣ “ዛሬስ ያለወትሯችሁ እንዴት ፈጥናችሁ ተመለሳችሁ?” አላቸው። 19.እነርሱም፣ “አንድ ግብጻዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ ቀድቶ በጎቻችንን አጠጣልን” አሉት። 20.አባታቸውም፣ ሴቶች ልጆቹን “የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? ጥሩትና ዐብሮን እንጀራ ይብላ” አላቸው። 21.ሙሴም ከሰውየው ጋራ ለመኖር ተስማማ፤ ራጉኤልም ልጁን ሲፓራን ዳረለት። 22.ሲፓራም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ሲል የልጁን ስም ጌርሳም ብሎ ጠራው። 23.ከብዙ ዓመት በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በባርነት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሣ ይጮኹ ነበር፤ ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያሰሙትም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ደረሰ። 24.እግዚአብሔርም የጩኸታቸውን ሲቃ ሰማ፤ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ የገባውንም ቃል ኪዳን ዐሰበ። 25.እግዚአብሔርም እስራኤላውያንን ተመለከተ፤ ስለ እነርሱም ገደደው።

ምዕራፍ 3

ሙሴና የሚንበለበለው ቍጥቋጦ

1.አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ። 2.እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለመቃጠሉን አየ። 3.ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ። 4.ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው።
ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው።
5.እግዚአብሔርም፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። 6.ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ። 7.ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ። 8.ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ። 9.አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብጻውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ። 10.በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”። 11.ሙሴ እግዚአብሔርን፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው። 12.እግዚአብሔርም፣ “እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው። 13.ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። 14.እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው። 15.ደግሞም እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛል፤’
“ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤
ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ
ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው።
16.“ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብጽ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ። 17.ስለዚህም በግብጽ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ’ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ። 18.“የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብጽ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ። 19.የግብጽ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በቀር መቼም እንደማይለቅቃችሁ ዐውቃለሁ። 20.ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቅቃችኋል። 21.“ይህ ሕዝብ በግብጻውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም። 22.እያንዳንዷ ዕብራዊት ከጎረቤቷም ይሁን ዐብራት ከምትኖረው ግብጻዊት የብርና የወርቅ ጌጣጌጦች እንደዚሁም ልብስ እንድትሰጣት ትጠይቅ። እነዚህንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታስጌጧቸዋላችሁ፤ ታለብሷቸዋላችሁም። በዚህም መንገድ የግብጻውያኑን ሀብት በእጃችሁ አግብታችሁ ትወጣላችሁ።

ወደ ገላትያ ሰዎች

ምዕራፍ 5

በክርስቶስ ያለ ነጻነት

1.ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ። 2.የምለውን አስተውሉ! ትገረዙ ዘንድ ብትፈልጉ፣ ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንተ እንደማይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችኋለሁ። 3.መገረዝ ለሚፈልግ ሁሉ ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት እንደ ገና ለእያንዳንዱ በግልጽ እናገራለሁ። 4.በሕግ ለመጽደቅ የምትጥሩ፣ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋ ርቃችኋል። 5.እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን ጽድቅ፣ በመንፈስ አማካይነት በእምነት ሆነን በናፍቆት እንጠባበቃለን። 6.በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑ፣ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፤ የሚጠቅመውስ በፍቅር የሚገለጽ እምነት ብቻ ነው። 7.ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ታዲያ ያሰናከላችሁ፣ ለእውነትስ እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? 8.እንዲህ ያለው ማባበል ከሚጠራችሁ የመጣ አይደለም፤ 9.“ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።” 10.የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ በጌታ እታመናለሁ። ግራ የሚያጋባችሁ ማንም ይሁን ማን፣ ፍርዱን ይቀበላል። 11.ወንድሞች ሆይ፤ እስከ ዛሬ ስለ መገረዝ የምሰብክ ከሆነ፣ ታዲያ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ፣ መስቀል ዕንቅፋት መሆኑ በቀረ ነበር። 12.ግራ የሚያጋቧችሁ ሰዎች የራሳቸውን መግረዝ ብቻ ሳይሆን ይጐንድሉ!

በመንፈስ መመላለስ

13.ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል። 14.ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሏል፤ ይኸውም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። 15.ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። 16.እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ እላለሁ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም። 17.ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን፣ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን ይመኛልና፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚጋጩ፣ የምትፈልጉትን አታደርጉም። 18.በመንፈስ ብትመሩ ግን፣ ከሕግ በታች አይደላችሁም። 19.የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ 20.ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ ዐድመኛነት፣ 21.ምቀኛነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው። አስቀድሜ እንዳልሁ፣ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 22.የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ 23.ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። 24.የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋራ ሰቅለውታል። 25.በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ። 26.እርስ በርሳችን እየተጐነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።