Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 5 · ቀን 21 (ሰኞ) 📅 Tikimt 2, 2019

ኦሪት ዘጸአት 1, 2, 3 · ወደ ገላትያ ሰዎች 5

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 1

1.ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ከቤተ ሰቡ ጋር ገባ። 2.ሮቤል፥ 3.ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ 4.ብንያም፥ ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር። 5.ከያቆብ ጕልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብፅ ነበረ። 6.ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም፥ ያም ትውልድ ሁሉ። 7.የእስራኤልም ልጆች አፈሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ አጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። 8.በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ። 9.እርሱም ሕዝቡን። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ 10.እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው አለ። 11.በብርቱ ሥራም ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ። 12.ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር። 13.ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው። 14.በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር። 15.የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ ሁለተኛይቱም ፉሐ የሚባሉትን የዕብራውያንን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ። 16.እናንተ የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት፤ ሴት ብትሆን ግን በሕይወት ትኑር። 17.አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው። 18.የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው። 19.አዋላጆቹም ፈርዖንን። የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው አሉት። 20.እግዚአብሔርም ለአዋላጆች መልካም አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ጸና። 21.እንዲህም ሆነ፤ አዋላጆች እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤቶችን አደረገላቸው። 22.ፈርዖንም። የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።

ምዕራፍ 2

1.ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። 2.ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። 3.ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። 4.እኅቱም የሚደረግበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጎበኘው ነበር። 5.የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው። 6.በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም። ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንድ ነው አለች። 7.እኅቱም ለፈርዖን ልጅ። ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን? አለቻት። 8.የፈርዖንም ልጅ። ሂጂ አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። 9.የፈርዖንም ልጅ። ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። 10.ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፥ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። 11.በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ። 12.ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። 13.በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም። ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ? አለው። 14.ያም። በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው። ሙሴም። በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል ብሎ ፈራ። 15.ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ። 16.ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውን ገንዳ ሞሉ። 17.እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። 18.ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ። ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ? አላቸው። 19.እነርሱም። አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ አሉ። 20.ልጆቹንም። እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ አላቸው። 21.ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። 22.ወንድ ልጅም ወለደች። በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። 23.ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። 24.እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። 25.እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።

ምዕራፍ 3

1.ሙሴም የዮቶርን የአማቱን የምድያምን ካህን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። 2.የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። 3.ሙሴም። ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ አለ። 4.እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ። ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ። 5.እርሱም። እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው። 6.ደግሞም። እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። 7.እግዚአብሔርም አለ። በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ 8.ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። 9.አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። 10.አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። 11.ሙሴም እግዚአብሔርን። ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። 12.እርሱም። በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ አለ። 13.ሙሴም እግዚአብሔርን። እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ። የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ። ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው። 14.እግዚአብሔርም ሙሴን። <<ያለና የሚኖር>>እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። <<ያለና የሚኖር>>ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። 15.እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ። የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። 16.ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ። እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ። መጐብኘትን ጐበኘኋችሁ፥ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ 17.ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ አልሁ ብሎ ተገለጠልኝ በላቸው። 18.እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትገባላችሁ። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ አሁንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ ትሉታላችሁ። 19.ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። 20.እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። 21.በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በሄዳችሁ ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤ 22.ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር ዕቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።

ወደ ገላትያ ሰዎች

ምዕራፍ 5

1.በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። 2.እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። 3.ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። 4.በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። 5.እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። 6.በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 7.በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? 8.ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።
9 -
10.የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። 11.ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። 12.የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። 13.ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። 14.ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። 15.ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። 16.ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። 17.ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። 18.በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። 19.የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ 20.መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ 21.መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 22.የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። 23.እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። 24.የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። 25.በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። 26.እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።
♫
Listen to the reading 4 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 1
ኦሪት ዘጸአት Chapter 2
ኦሪት ዘጸአት Chapter 3
ወደ ገላትያ ሰዎች Chapter 5
Swipe to browse chapters
Listen 4