ሳምንት 1 · ቀን 2 (ማክሰኞ)
📅 Meskerem 5, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 3, 4, 5 · የማርቆስ ወንጌል 2
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 3
የሰው ውድቀት
1.እባብ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሏልን?” አላት። 2.ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ 3.ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።” 4.እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ 5.ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” 6.ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከርሷም ጋራ ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። 7.የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ። 8.ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሚስቱ ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። 9.እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው። 10.አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ። 11.እግዚአብሔርም፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። 12.አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋራ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። 13.እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት።እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች። 14.እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣
“ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ
ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ
እየተሳብህ ትሄዳለህ፤
ዐፈርም ትበላለህ። 15.በአንተና በሴቲቱ፣
በዘርህና በዘሯ መካከል፣
ጠላትነትን አደርጋለሁ፤
እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤
አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” 16.ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤
“በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤
በሥቃይም ትወልጃለሽ፤
ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤
እርሱም የበላይሽ ይሆናል።” 17.አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣
“ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ
ምግብህን ጥረህ ግረህ ከርሷ ታገኛለህ። 18.ምድርም እሾኽና አሜከላ
ታበቅልብሃለች፤
ከቡቃያዋም ትበላለህ። 19.ከምድር ስለ ተገኘህ፣
ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ
ድረስ
እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤
ዐፈር ነህና
ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” 20.አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት። 21.እግዚአብሔር አምላክ ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። 22.ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። 23.ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ 24.ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ ከዔድን በስተምሥራቅ አኖረ።
ምዕራፍ 4
ቃየንና አቤል
1.አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። 2.ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች።አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። 3.በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። 4.አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎቹ መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ 5.በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ። 6.እግዚአብሔርም ቃየንን እንዲህ አለው፤ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? 7.መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።” 8.ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ “እስኪ ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ” አለው፤ በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም። 9.ከዚያም፣ እግዚአብሔር ቃየንን፣ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው።
ቃየንም፣ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ሲል መለሰ። 10.እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ምንድን ነው ያደረግኸው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። 11.እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። 12.ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” 13.ቃየንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። 14.እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” 15.እግዚአብሔር ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት። 16.ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ። 17.ቃየን ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ሔኖክን ወለደች። ቃየን የቈረቈረውን ከተማ በልጁ ስም ሔኖክ ብሎ ጠራው። 18.ሔኖክ ኢራድን ወለደ፤ ኢራድም መሑያኤልን፣ መሑያኤልም ማቱሣኤልን፣ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። 19.ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የአንደኛዋ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛዋም ሴላ ነበር። 20.ዓዳ ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ከብት አርቢዎች አባት ነበረ። 21.ወንድሙም ዩባል ይባላል፤ እርሱም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበረ። 22.ሴላም ደግሞ ቱባልቃይን የተባለ ወንድ ልጅ ነበራት፤ እርሱም ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እየቀረጸ የሚሠራ ነበር። የቱባልቃይን እኅት ናዕማ ትባል ነበር። 23.ላሜሕ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤
“ዓዳና ሴላ ሆይ ስሙኝ፤
የላሜሕ ሚስቶች ሆይ አድምጡኝ፤
አንድ ሰው ቢያቈስለኝ፣
ጕልማሳው ቢጐዳኝ፣ ገደልሁት፤ 24.ቃየንን የሚገድል ሰባት ጊዜ ቅጣት ካገኘው፣
የላሜሕ ገዳይማ ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ያገኘዋል።” 25.አዳም እንደ ገና ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ” ስትል ስሙን ሴት ብላ ጠራችው። 26.ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው።
በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ።
ምዕራፍ 5
ከአዳም እስከ ኖኅ
1.የተጻፈው የአዳም የትውልድ ሐረግ እንደሚከተለው ነው።እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው በራሱ አምሳል አበጀው፤ 2.ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ባረካቸው፤ በተፈጠሩም ጊዜ “ሰው” ብሎ ጠራቸው፦ 3.አዳም፣ ዕድሜው
130 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እርሱን ራሱን የሚመስል ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው። 4.ሴት ከተወለደም በኋላ፣ አዳም
800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ 5.አዳም በአጠቃላይ
930 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 6.ሴት፣ ዕድሜው
105 ዓመት ሲሆን ሄኖስን ወለደ፤ 7.ሴት ሄኖስን ከወለደ በኋላ
807 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 8.ሴት በአጠቃላይ
912 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 9.ሄኖስ፣ ዕድሜው
90 ዓመት በሆነ ጊዜ ቃይናንን ወለደ፤ 10.ሄኖስ ቃይናንን ከወለደ በኋላ
815 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 11.ሄኖስ በአጠቃላይ
905 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 12.ቃይናን፣ ዕድሜው
70 ዓመት ሲሆን መላልኤልን ወለደ፤ 13.ቃይናን መላልኤልን ከወለደ በኋላ
840 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 14.ቃይናን በአጠቃላይ
910 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 15.መላልኤል፣ ዕድሜው
65 ዓመት በሆነ ጊዜ ያሬድን ወለደ፤ 16.መላልኤል ያሬድን ከወለደ በኋላ
830 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 17.መላልኤል በአጠቃላይ
895 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 18.ያሬድ፣ ዕድሜው
162 ዓመት ሲሆን ሔኖክን ወለደ፤ 19.ያሬድ ሔኖክን ከወለደ በኋላ
800 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 20.ያሬድ በአጠቃላይ
962 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 21.ሔኖክ፣ ዕድሜው
65 ዓመት በሆነ ጊዜ ማቱሳላን ወለደ፤ 22.ሔኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋራ በማድረግ
300 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 23.ሔኖክ በአጠቃላይ
365 ዓመት ኖረ፤ 24.ሔኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋራ አደረገ፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም። 25.ማቱሳላ፣ ዕድሜው
187 ዓመት ሲሆን ላሜሕን ወለደ፤ 26.ማቱሳላ ላሜሕን ከወለደ በኋላ፣
782 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ 27.ማቱሳላ በአጠቃላይ
969 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 28.ላሜሕ፣ ዕድሜው
182 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ ልጅ ወለደ። 29.ስሙንም “እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከልፋታችንና ከጕልበታችን ድካም ያሳርፈናል” ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው። 30.ላሜሕ ኖኅን ከወለደ በኋላ፣
595 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 31.ላሜሕ በአጠቃላይ
777 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ። 32.ኖኅ ዕድሜው
500 ዓመት ሲሆን ሴምን፣ ካምንና ያፌትን ወለደ።
የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 2
ኢየሱስ ሽባ ፈወሰ
2፥3-12 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥2-8፤ ሉቃ 5፥18-26
1.ኢየሱስ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም እንደ ተመለሰ፣ ወደ ቤት መግባቱን ሕዝቡ ሰማ።
2.ስለዚህ ከበሩ ውጭ እንኳ ሳይቀር ስፍራ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ሰበከላቸው።
3.ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እርሱ አመጡ።
4.ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ እርሱ ወዳለበት ሊያቀርቡት ስላልቻሉ፣ የቤቱን ጣራ እርሱ ባለበት በኩል ነድለው ቀዳዳ በማበጀት ሽባው የተኛበትን ዐልጋ በዚያ አወረዱ።
5.ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።
6.በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ስለዚህ ነገር በልባቸው እያሰላሰሉ፣
7.“ይህ ሰው እንዴት እንዲህ ይላል? በአምላክ ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ እኮ ነው! ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” ብለው አሰቡ።
8.ኢየሱስም ወዲያው የሚያስቡትን በመንፈሱ ተረድቶ፣ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ?
9.ሽባውን፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና፣ ‘ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል?
10.ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣
11.“ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
12.እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ዐልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ በስፍራው የነበሩትም ሁሉ በሁኔታው በመደነቅ፣ “የዚህ ዐይነት ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም!” በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ።
የሌዊ መጠራት
2፥14-17 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥9-13፤ ሉቃ 5፥27-32
13.ኢየሱስም ዳግም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጣ፤ ሕዝቡም በብዛት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም አስተማራቸው።
14.በዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መሰብሰቢያው ስፍራ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።
15.በሌዊም ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች ተከትለውት ስለ ነበር፣ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ዐብረው ይመገቡ ነበር።
16.የፈሪሳውያን ጸሐፍት ከኀጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋራ ሲበላ ባዩት ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋራ ለምን ይበላል?” ሲሉ ጠየቋቸው።
17.ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው።
ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ
2፥18-22 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥14-17፤ ሉቃ 5፥33-38
18.የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።
19.ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ዕድምተኞቹ ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋራ እያለ ሊጾሙ አይችሉም፤
20.ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ።
21.“በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፣ አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሰፋል።
22.እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ የሚያስቀምጥ የለም፤ ይህ ከተደረገማ የወይን ጠጁ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም አቍማዳውም ይበላሻሉ። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ መቀመጥ ያለበት በአዲስ አቍማዳ ነው።”
ኢየሱስ የሰንበት ጌታ ነው
2፥23-28 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥1-8፤ ሉቃ 6፥1-5
3፥1-6 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥9-14፤ ሉቃ 6፥6-11
23.በሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ሲያልፍ፣ ዐብረውት በመጓዝ ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።
24.ፈሪሳውያንም፣ “እነሆ፤ በሰንበት ቀን ለምን ያልተፈቀደውን ነገር ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት።
25.እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት በተራበና የምግብ ፍላጎት በጸናበት ጊዜ ዐብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋራ ያደረገውን አላነበባችሁምን?
26.በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ካህናት ብቻ እንዲበሉት የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።”
27.ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፤
28.ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው።”